Thursday, June 27, 2013


ሕዝባዊ ንቅናቄያችን የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር ያደርጋል!!

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት ህዝባዊ ንቅናቄ የትግል ስልት በመንደፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን በይፋ መግለጹ አይዘነጋም፡፡ የህዝባዊ ንቅናቄው የመጀመሪያ የአደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍም ሰኔ 30/10/2005 በጎንደር ከተማ ይደረጋል፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት በሚደነግገው መሰረትም ፓርቲው ከህዝቡ ጋር የሚያደርገውን ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር ከተማ ማወቅ ለሚገባው አካል የፓርቲያችን መዋቅር አሳውቆ ወደ ቅስቀሳ ገብተዋል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ ላይም በጎንደር እየተፈጸመ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሰዎችን በአደራ ማሰር፣ ለሱዳን ከህዝቡ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ መሬት መሰጠቱን፣ በነጋዴዎች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር፣ ለስራ የደረሱ ወጣቶች የፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር ስራ የማያገኙበትን ሁኔታ፣ በዘር ላይ የተመሰረተን ማፈናቀልና የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ህዝቡ የተቃውሞ ድምጹን በነቂስ ወጥቶ ያሰማል፡፡ እንዲሁም የጸረ ሽብር ህጉ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ እንዲሰረዝ ይጠየቃል፡፡ ብዙ ሺ የከተማው ኗሪዎችም የተቃውሞ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉን በጎንደር ከሚገኙ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ጋር የተሳካ ለማድረግ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ቢሮ አስተባባሪ አባላት የተላኩ ሲሆን የቅስቀሳ ስረቸውንም ጀምረዋል፡፡ ቅዳሜም ሁለተኛው ቡድን ወደ ጎንደር ያቀናል፡፡ የፓርቲያችን ስራ አስፈጻሚ፣ የብሄራዊ ምክር ቤትና በየመዋቅሩ ያሉ አባላቶቻችን በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለመገኘት ወደ ጎንደር ያመራሉ፡፡

ሰላማዊ ሰልፉ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ጎንደር ከሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተነስቶ ወደ መስቀል አደባባይ በማምራት በመስቀል አደባባይ በሚደረግ ልዩ ልዩ ፕሮግራም የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በጎንደር መስቀል አደባባይ ለሚገኘው ህዝብ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች የሰላማዊ ሰልፉን ዓላማ የሚገልፅ ንግግር ያደርጋሉ፡፡

ፓርቲያችን አንድነትም የሦስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄያችንን ይፋ ካደረግን ጀምሮ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የሚዲያ ተቋማት፣ የፀረ-ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ፔቲሽን ለፈረሙትና ከጎናችን ለቆሙ ታዋቂ ግለሰቦች በአክብሮት ምስጋና እያቀረብን አሁንም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ሰኔ 20 ቀን 2005 ዓ.ም

አዲስ አበባ