Sunday, January 25, 2015

10298794_640348846050053_3108728034139348229_n

ሰላማዊ ትግላችን በምርጫ ቦርድ ህገ-ወጥ ውሳኔና በአገዛዙ የኃይል ርምጃ አይቀለበስም! – በሰሜን  አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር

በዛሬዉ ዕለት ጥር 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ፤ በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ የደረሰዉን ዘግናኝ ድብደባ፣ እስርና እንግልት በጥብቅ እንቃወማለን። የመንግሥት አስተዳደር ወይም ህግ አለ በሚባልበት አገር እጅግ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የደረሰው ድብደባ የተጀመረዉን ሰላማዊ ትግል ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የታለመ ነዉ ብለን አናምናለን። አገዛዙ አንድነት ፓርቲን እንደ ባዕድ ወይም ጠላት በሚመስል መልኩ ታጣቂ ኃይሎችን በብዛት በማሠማራት በሠልፈኞች ላይ ድብደባና እንግልት ፈፅሞባቸዋል።
አገዛዙ በተደጋጋሚ በህጋዊ ፓርቲዎች አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ ግድያና ድብደባ አንዲሁም ዘረፋ በማድረግ መንግሥታዊ ዉምብድናዉን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። አንድነት ከአሁን በፊትም ከፍተኛ መሥዋዕትነት እየከፈለ፣ እልህ አስጨራሽ መራር ሰላማዊ ትግሉን እየመራ ይገኛል። ህወሃት መራሹ አምባገነን የዘውግ መንግሥት በፈጠራቸዉ አሥመሣይ ተቋማት በመገልገል በእጅ አዙር በህዝቡና በሰላማዊ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ውምብድና እየፈፀመ ይገኛል። ምርጫ ቦርድ፣ፖሊስና የደህንነት ኃይል፤እንዲሁም አሥተዳደሩ ባጠቃላይ አንድነትንና ሌሎች አጋር ፖርቲዎችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፉት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።
አገዛዙ ከህገ-ወጥ ተግባሩ ታቅቦ መንግሥታዊ ሥነ ምግባር እንዲዝና ሰላማዊ ፖርቲዎችን የማጥፋትና የማሳደዱን ክፉ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነና የሰላማዊ ትግሉ በር ከተዘጋ ህዝቡ አማራጭ መፍትሄ መፈለጉ ስለማይቀር ለሚፈጠረዉ አገራዊ ቀዉስ የስርዐቱ ኀላፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ አንጠራጠርም።

በመጨረሻም የአንድነት አመራሮች የአካሄዱትን ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ አድናቆታችንን እየገለጽን፤ ይህን ዘግናኝ ግፍና በደል ለማስቆም፣ እንዲሁም የአገዛዙን አፈናና ጭቆና ለመቋቋም፣ ብሎም የህዝቡን ልዕልና ለማስከበር ኢትዮጵያዉያን ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅተዉ በመታገል በህዝባዊ ኃይል አገዛዙን ከማስወገድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም። ስለሆነም ትግላችንን በህብረት አጠናክረን ህዝባዊ ትግሉን ለማቀጣጠል ሁላችንም ቆርጠን እንነሳ፦

በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚደረገዉ ድብደባና ግድያ በአስቸኳይ ይቁም!
ህዝባዊ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል!

በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
የሥራ አመራር ቦርድ

Saturday, January 17, 2015

ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!!
      

ጉዳዩ፥  በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና በአንድነት ፓርቲ መካከል    የተፈጠረውን ውዝግብ በተመለከተ፡፡

እንደሚታወቀው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት ከምርጫ ቦርድ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ በ 4 ቀን ውስጥ እንዲጠራና የፓርቲውን መሪ በድምፅ አሠጣጥ መመሪያው መሠረት እንዲመርጥ ስለተገደደ አንድነት ፓርቲም በሆደ ሰፊነት በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ባያምንበትም ሕግ ለማክበርና የሠላማዊ ትግሉን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ስለሚረዳ በሌለ አቅሙ በ 4 ቀን ውስጥ በአስቸኳይና በታላቁ በገና በዓል ሣምንት የጉባዔ አባላትን ከክ/ሃገር ጭምር ጉባዔ ጠርቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፋ በ 4 ቀን ጉባዔ እንዲጠራ ካዘዘ በኋላ በጉባዔው ተገኝቶ ምርጫውን ታዝቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጋብዞ ሣይገኝ ቀርቷል፡፡ ይህ ዓይነት የምርጫ ቦርድ ሕገ-ወጥነት በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ምርጫ ቦርድ አሁንም እጅግ በጣም በሚያሳፍርና ይሉኝታ በሌለው አካሄድ አንድነት ፓርቲንና መኢአድን በድጋሜ ጉባዔ እንዲጠሩ ሕገ-ወጥ ትዐዛዝ ለማስተላለፍ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን ውስጥ ጉዳይ የመፈትፈት፣ ውሣኔ የመቀልበስ፣ እንዲሁም የፓርቲዎችን አመራር የማፅደቅ ወይም ያለማጵደቅ መብት ጨርሶ ሊኖረው አይገባም፡፡ ምከንያቱም እንደዚህ ዓይነት ጣልቃ ገብነት ካለ የፓርቲዎች የበላይ አካል የሚሆነው የአባሎቻቸው ጠቅላላ ጉባዔ ትርጉም አልባ ይሆናልና፡፡
አንድነት ፓርቲ በምጫ ቦርድ በድጋሜ የተላለፈውን ጉባዔ የመጥራት ትዕዛዝ እንደማይቀበለው መግለፁን ስንቀበል፤ እኛም የአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር ሙሉ በሙሉ እንደምንደግፍ እናረናገግጣለን፡፡ ምርጫ ቦርድ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ ለአገዛዙ ወገናዊነትን ለማረጋገጥ በአስተዳደሩ ኃላፊዎች በመታዘዝ፤ በአንድነት ፓርቲና በሌሎች ተቃዋሚ አጋር ፓርቲዎች
የሚያደርገውን ሕገ-ወጥነት አስተዳደራዊ ክፉ ሥራ አጥብቀን እንቃወማለን! አንቀበለውም:: አገዛዙ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ ከፈለገ ህጋዊ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በህገ-ወጥነት ሣይሆን በስርዓት፣ በአግባቡ የጨዋታ ሜዳውን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ የተደጋጋሚ ጉባዔ ጥሩ ትዕዛዝ ህገወጥ ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም፡፡ አገዛዙ እንደዚህ ዓይነት እጅግ የዘቀጠ ፀያፍ ስራ
ውስጥ ተነክሮ ያለው መጪውን ብሔራዊ ምርጫ ያለተቀናቃኝ ብቻዉን ተወዳድሮ ለማሸነፍ ካለው ጭፍን ፍላጐት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም ግን ይህ አካሄዱ ሃገሪቱን ወደ ባሰ ምስቅልቅል ይወስዳታል እንጅ ሌላ ፋይዳ የለውም፡ በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ማለትም መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ መድረክና፣ ሌሎችም ፓርቲዎች ተቀራርበው ትግሉን በጋራ እንዲመሩት ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ፓርቲዎቹ አገዛዙን በመቃወም ለሚያደርጓቸው ማንኛውም የሠላማዊ እንቅስቃሴዎች ከጐናቸዉ እንደምንቆም በዚህ እጋጣሚ ማሣወቅ እንወዳለን፡፡ አንድነት ፓርቲ በሚያደርጋቸው የትብብር ጥሪዎችና የአመራር ስልቶች በተናጠልም ወይም ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር ለሚያደርጋቸው ትግሎች ሙሉ በሙሉ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብም የአገዛዙን ተንኮል በመረዳት ከአንድነትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጐን በመሰለፍ የነፃነት ትግሉ እንዲያፋጥን ጥሪ አናቀርባለን፡፡