ቶሮንቶ፤ ከአንድነትና ከነቀምት ከተማ ጎን ይቆማል !!
የአንድነት ቶሮንቶ የድጋፍ ሰጪ ማህበር መግለጫ
ሚያዚያ፤ 2014፤ ቶሮንቶ፤ ኦንቴርዮ
አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፤ (ከዚህ በኋላ "አንድነት")፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ፤ ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አዲስ
አበባ የሚያበቃ፤ በ17 ከተሞች የሚደረግ፤ የኑሮ ውድነትን፤ የመሬት ባለቤትንትን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈናን፤ የሚመለከቱ
የተቃውሞ ሰልፎችን አሰናድቷል፡፡
የመጀመሪው ሰልፍ፤ እሁድ መጋቢት 28 ቀን በአዲስ አበባ እንዲደረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የአዲስ
አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት በፈጠረው ስንኩል ምክንያት ሰልፉ ተጨናግፏል፡፡ በተመሳሳይ ቀን የተጠራው
የደሴ ሰልፍ ግን፤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
የአዲስ አበባው ተለዋጭ ሰልፍ፤ ለእሁድ፤ ሚያዚያ 5 ቀን የተቀጠረ ሲሆን፤ ሰልፉ የተሳካ እንደሚሆን
ተስፋ እናደርጋለን፡፡
አንድነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚደርጋቸውን ሰልፎች በገንዘብ ለመርዳት፤ በሲያትል፤
አትላንታ፤ ላስ ቬጋስና ሌሎች ከተሞችም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቃል ገብተዋል፡፡ ቅዳሜ፤ እንደፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ማርች
29 ቀን የተሰበሰበው የቶሮንቶ አንድነት ድጋፍ ሰጪ ማህበርም፤ የነቀምትን ከተማ ሰለፍ ለመርዳት መወሰኑን ሲያስታውቅ በታላቅ ኩራት
ነው፡፡
አንድነት ቶሮንቶ፤ ለነቀምቱ ሰልፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ቅዳሜ
ኤፕሪል 26 ቀን፤ 2014 ዓ.ም.፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3pm ሰኣት ጀምሮ፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ በሚገኘው ሂሩት ካፌ፤ አጋርነት ለነቀምት፤ የተሰኘ፤ መደበኛ ያልሆነ የአንድነት
መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ በቶሮንቶና አካባቢው የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዝግጅቱ ላይ እንድትገኙና የበኩላችሁን የገንዘብ አስተዋጽኦ
እንድታደርጉ አንድነት ቶሮንቶ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አንድነት ቶሮንቶ፤ አገር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የተለያዩ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎችን
አልፈው የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሰልፋቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት መሰናከል የለበትም የሚል እምነት አለው፡፡
ስለዚህም፤ በዚህ መደበኛ ባልሆነ፤ የአብረን እንዋል ዝግጅት ላይ በመገኘት፤ የበኩልዎን የገንዘብ ልገሳ እንዲያደርጉ ጥሪ እያደረገ፤
በእለቱ በአካል መገኘት ካልቻሉም የገንዘብ ልገሳዎን በሌላ ሰው መላክ እንደሚችሉ፤ እንዲሁም ችሮታዎን በአንድነት የባንክ ሂሳብ
Unity for Human Rights and Democracy: TD Trust; የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 12682 0041 0883
5209213፡ ማስገባት እንደሚችሉ ይጠቁማል፡፡
በዚህ አጋጣሚም፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት (UDHR) ወይም
በተለምዶ ዩዲጄ ቶሮንቶን
እንዲተዋወቁና፤ በአንድነት አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ
የሚከተለውን ማስታወሻ እናክላለን፡፡
አንድነት ቶሮንቶ ማነው፤ ዋና ዓላማው፤
አንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት (Unity for Democracy and Human
Rights) ፤ በኦንቴሪዮ ግዛት የተመዘገበ በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ላይ የሚሰራ፤ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት
ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም፤ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግና፤ ኢትዮጵያዊያ ካናዳዊያን
በካናዳ ውስጥ የተሳካ ህይወትና ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማበረታታትና መድረክ መፍጠር ነው፡፡
እንድነት ቶሮንቶ እስካሁን የሰራቸው ስራዎች፤
አንድነት ከተመሰረተ ጀምሮ፤ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊን፤ የድጋፍና የምክር አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ካናዳዊያን፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተቃውሞ ሰልፎች፤ በገንዘብ ድጋፍና በዲፕሎማሲ እንዲሳተፉ መድረኮችን ፈጥሯል፡፡
ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ መሪዎች በቶሮንቶና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ከካናዳ ባለስልጣናት ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የተነሰራፋውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለካናዳ መንግስት አጋልጧል፡፡ የካናዳ መጤዎችና ስደተኞች ጉዳዮች ባለስልጣን (Immigration
and Refugee Board of Canada)፤ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች፤ የጽሁፍ
ማብራሪያዎችንና አስተያየቶችን ሰጥቷል፡፡ ለብዙ ስደተኞች የሕይወት ስልጠናዎችንና የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የበጎ
ፈቃድ መድረኮችን ፈጥሯል፡፡ በተለይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸው፤ የካናዳን ጥበቃ እንዲያገኙና
ተረጋግተው እንዲኖሩ፤ ባደረገውና በሚያደርገው በገንዘብ የማይተመን ድጋፍ ይኮራል፡፡
አንድነት ቶሮንቶ አሁን የሚሰጣቸው አገልግሎቶች፡
ያለፉትን አመታት ስራ የገመገመው የአንድነት ቶሮንቶ ስራአስፈጻሚ አካል፤ ድርጅቱ ካለፉት ሁለት አመታት
ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ቀዝቀዝ ብሎ እንደነበር አምኖ፤ በቀጣዮቹ ወራት ከላይ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች አስፍቶና አጠናክሮ መቀጠል
እንዳለበት ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት፤ የሚከተሉትን አገልግሎቶች ለማግኘት ወይም ለመስጠት የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን፤ አንድነትን
እንዲያገኙ ወይም እንዲጎበኙ
ይበረታታሉ፡፡
ለስደተኞችና አዲስ መጥ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላላ የምክር አገልግሎት መስጠት፤ የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ፤
የበጎ ፍቃድ ስራዎችን (volunteering) መስራት ለሚፈልጉ ሰዎች መድረኮችን ማመቻቸት፤ የትምህርት ነክ መረጃዎችንና መንገዶችን
መጠቆም፤ የካናዳን እወቁ ምክርና የሕይወት ልምድ ልውውጦችን ማዘጋጀት፤ ስደተኞችን መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች
ጋር ማስተዋወቅ፤ የስራ ጥቆማዎችን መስጠትና ሌሎች መሰል ተግባራትን ማከናወን ናቸው፡፡
ወደካናዳ የመጣ፤ ወይም መምጣት የሚያስብ፤ ዘመድ ወይም ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ካለዎት ከላይ ከተዘረዘሩት፤
ከስራ፤ ከትምህርት እድል፤ ከስደተኝነት ጋር በተያያዘ ጠቅላላ የምክር አገልግሎቶችን የሚፈልጉ ከሆነ፤ አንድነትን ይጎብኙ፡፡ ለተጨማሪ
ዝርዝር አገልግሎቶችና መረጃዎች ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ፤ እሁድ ከሰዓት በኋላ በአካል በጽህፈት ቤታችን በመገኘት፤ ወይም ከታች በተጠቀሱት
የመገናኛ መንገዶች እንዲያገኙን እናስታውቃለን፡፡
አንድነትን ቶሮንቶን ለማግኘት፤
ኢሜል፤ unityforhumanrights@gmail.com
ትዊተር፤ @AndinetToronto
ስልክ፤ 416 422
2962/416 985 6599
የጽህፈት ቤት አድራሻ፡ B2- 2017 Danforth Avenue, Toronto, ዳንፎርዝ ላይ፤ ከዉድባይን
ባቡር ጣቢያ በስተምስራቅ 50 ሜትር ራቅ ብሎ፤ ከዘመን እንጀራ መደብር
በተቃራኒ፤ ከትብብር መረዳጃ እድር አጠገብ፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት፤ የህዝብ ግንኙነት ክፍል፤ ሚያዚያ፤ 2006/2014