Unity for Human Rights and Democracy is a volunteer based, not for profit community organization, striving to empower Ethiopian-Canadians to advocate for Human Rights,Democracy and Good Governance in Ethiopia.
Friday, July 11, 2014
ትግሉ የጥቂቶች ሳይሆን የሚሊዮኖች ሆኗል።
የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር
በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉጉትና ምኞት ፣ ልጆችዋ ከርሷ የሚሰደዱባት ሳይሆን የተሰደዱት ተመልሰው ለሌሎች መጠጊያ የምትሆን፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ጾታና መደብ ሳይባል ለሁሉም እኩል የሆነች፣ አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ነገር ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገዛዙ እያየን ያለነው፣ ልብን የሚያደማና የሚያቆስል ነው። በስድሳዎቹ ከነበረው የደርግ ስርዓት በባሰ፣ አገዛዙ ሕዝባችን ላይ የግፍ ቀንበር ጭኖ ፣ የጸረ-ሽብርተኝነት ሕግ በሚል ሰበብ ሰላማዊ ዜጎችን እያሸበረ ነው።
የአንድነት ፓርቲ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ በሚል መርህ፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፣ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲቆም በመቀስቀስ፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ድርጅታዊ ሥራ በመስራት፣ በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረገ እንዳለ ይታወቃል። በቅርቡም ከመኢአድ ጋር የቅድመ ዉህደት ስምምነትን በመፈረም የዴሞክራቲክ ካምፑን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ ይቻል ዘንድ፣ ትልቅ ሥራ ተሰርቷል። እነዚህ አገረ ሰፊ እንቅስቃሴዎች፣ አገዛዙን አስደግጠውታል ፣ አሸብረውታልም። ሥር እየሰደደ በመጣዉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድምጹን እያሰማ የመጣዉን የሕዝብ ጥያቄ፣ በአክብሮት ከመመለስ ይልቅ፣ አገዛዙ ከሕዝብ ጋር መላተምን መርጧል። በሕዝብ ዘንድ ከበሬታና ተወዳጅኘት ያላቸውን፣ በሰላማዊነታቸውና በአገር ወዳድነታቸው የሚታወቁትን ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ ወጣት ጋዜጠኞችን እና ብሎገሮች፣ የዲሞክራሲ አክቲቪስቶችን በማሰርና በማስፈራራት ፣ ለነጻነት የሚደረገዉን እንቅስቅሴ ለመግታት ብሎም የሕዝቡን ድምጽ ለማፈን ደፋ ቀና እያለ ነው።
በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ግብረ ኃይል፣ የመኢአድና አንድነት የውህደት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ም/ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አባልና ታዋቂ ብሎገር አቶ አብርሃ ደስታ እና ወገኖችን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ እስርቤት ጥሎ ማሰቃየቱን አገዛዙ በሰፊው መያያዙ በጣም አሳዝኖናል። አስቆጥቶናልም።
የተቀናጀ ህገወጥ ድርጊቶችን የምንኮንነዉና የምናወግዘው ሲሆን፣ አገዛዙም በሕዝቡ ላይ ጦርነት ማወጁን በገሃድ የሚያመላክት እንደሆነ ለማየት ችለናል።በአሁኑ ጊዜ የሕዝቡ ስነልቦና ተቀይሯል። ኢትዮጵያዉያን ግፍን ለመሸከም የሚችሉበት ትከሻ የላቸውም። ጥቂት ወጣት የሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን በማሰር፣ ሕዝቡን አስፈራርቶና መብቱን ረግጦ የመግዛት ዘመን አልፏል። ትግሉ የጥቂቶች ሳይሆን የሚሊዮኖች ሆኗል። በአገር ውስጥና ከአገር ዉጭ ሕዝባዊና ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻው ይጧጧፋል። አገዛዙ በያዘው ብረትና በፈረንጆች ድጋፍ ይመካሉ። እኛ ግን በዉስጣችን ባለው ኢትዮጵያዊ ወኔ፣ በገዛ ክንዳችን እና በፈጣሪ ረድኤት እንመካለን። አገዛዙ ጥላቻን እና ጭካኔን፣ ዘረኝነትን እና መከፋፈልን ይሰብካል። እኛ ግን ፍቅርን እና መቻቻልን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን እንሰብካለን።
በርግጥ የታሰሩ ወጣት የፖለቲካ መሪዎች ወደ ወህኒ መዉረድ ሁላችንንም ያሳዘነና ያስቆጣ ቢሆንም ታሳሪዎቹ ግን ፣ እንደ ክብር ነው የሚያዩት። የነርሱን መፈታት እና ለነርሱም አጋርነታችንን ማሳየት ከፈለግን፣ ማድረግ የሚኖርብን ፣ ከዝምታ ወጥተን፣ የፍርሃትን ካባ አዉልቀን፣ ከሚሊዮኖች አንዱ መሆን ነው። ቆመን፣ ተዋርደን፣ ፈርተን እና ተሸማቀን ከመኖር፣ የሕሊና ነጻነት አግኝተን በአካል መታሰር ይሻለናልና።
በአገር ቤት ያሉ የፖለቲካ መሪዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት በዚህ አጋጣሚ እያደነቅን፣ ከነርሱ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ከመቼዉም ጊዜ በላይ የሰላም ትግሉን እንደምንደግፍ ለማረጋገጥ እንወዳለን። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከሽብር ድርጊቶቹ በአስቸኳይ ተቆጥቦ፣ አራቱ ወጣቶችን ጨምሮ የታሰሩ የሕሊና እስረኞችን በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ የሕዝብን ጥያቄ ለራሱ ሲል እንዲያከብር እናስገነዝባለን። አገር በዱላና በጡንቻ አትገነባም። አገር የምትገነባው በፍቅር፣በመቻቻልና በመግባባት ነው። የአገዛዙ መሪዎች ልቦናቸውን ለፍቅር ያስገዙ እንላለን። እምቢ ካሉ፣ ካከረሩ ግን ታሪክ እንደሚያስተምረው አወዳደቃቸው እጅግ ታላቅ እና አስከፊ እንደሚሆን ልናስጠነቅቃቸው እንወዳለን።
ኢትዮጵያዉያን ከተባበርን፣ ሁላችንም የድርሻችንን ለማበርከት ከተነሳን፣ ከሚሊዮኖች አንዱ ከሆንን፣ አገዛዙ ፈለገም አልፈለገም የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈታሉ። የተሰደዱ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። የአገራችንን ትንሳኤ እናውጃለን።
የሰላም ትግሉ ተቀናጅቶና ተጠናክሮ ይቀጥላል!!!
July 11, 2014
Subscribe to:
Posts (Atom)