ወርሃዊ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁነቶች -ሚያዝያ 2009
እነደተለመደው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችና የህግ የበላይነት ጉዳይ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ አልመጣም፡፡ በወርሃ ሚያዝያ የተከናወኑ ዋና ዋና ሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዪችን በአጭሩ እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡
1. በእነ ጉርሜሳ አያኖ/በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎች ትርጉም ባለመቅረቡ ተከሳሾች እየተጉላሉ ነው
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለሚያዚያ 2, 2009 ዓ.ም አቃቤ ህግ በማስረጃነት ያቀረባቸው በኦሮምኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተሰሙ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎችን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቶት ነበር፡፡
ሆኖም እንዲተረጎሙ የተላኩትን 3ት ሲዲዎች ለመተርጎም ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው እና ባለሙያዎች የስራ መደራረብ ስላለባቸው ፍ/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የሚገልፅ በ29/7/2009 ከኢብኮ የተፃፈ ደብዳቤ መቅረቡን ዳኞች በመግለጽ ትርጉሙ እንዳልደረሳቸው አሳውቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎም አቃቤ ህግ የእንግሊዝኛና የኦሮምኛ አስተርጓሚ ተፈልጎ ማስረጃው በድጋሚ በችሎት እየታየ እንዲተረጎም ጠይቋል።
ተከሳሾች ግን የትርጉም ስራውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጠ መሆኑ ገልፀው፤ አቃቤ ህግ ሃላፊነቱን እንዳልተወጣና ማስረጃዎቹን በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ ማቅረብ እንዳልተፈለገ ተቆጥሮ ማስረጃው ውድቅ እንዲደረግና በቀረቡ ማስረጃዎች ብይን እንዲሰጥ አመልክተዋል። ተከሳሾች በአቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን በአግባቡ ባለማቅረቡ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ስለመሆናቸውም ለፍርድ ቤቱ ገልጸው ነበር፡፡
ጉዳዩን የሚያየው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በበኩሉ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሚመለከተው ሃላፊ ሁለት አስተርጓሚዎችን(አንድ የኦሮምኛ እና አንድ የእንግሊዘኛ ቋንቋ) ይዞ ሚያዚያ 5, 2009 ዓ.ም እንዲቀርብ ጥብቅ ትእዛዝ በመስጠት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
ሆኖም በዚሁ ቀጠሮ (ሚያዝያ 5/2009) ኢብኮ የድምፅ ከምስል አስተርጓሚ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ በዚህ ቀጠሮ ከኢብኮ ለምን ትርጉምን እንዳልሰሩ ለማስረዳት የተላኩ የስራ ኃላፊ፣ "ጉዳዩ ሴንሴቲቭ ነው፤ የቋንቋ ብቻ ጉዳይ ሳይሆን የህግ ጉዳይ ነው።" በማለት ለፍ/ቤት ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ከፍ/ቤት ተልከው የሚሄዱትን ፓስተኞች አልቀበልም እያሉ የተቋሙ (ኢብኮ) ሰራተኞች እንደሚያስቸግሯቸው ጠቅሰው ባጠቃላይ ተቋሙ የፍ/ቤት ትእዛዞችን ከዚህ ቀደም ያልፈፀመበት አግባብ ምክንያታዊ እንዳልሆነ በመናገር ከዚህ ቀደም የሆነውን በማስጠንቀቂያ እንዳለፏቸው ገልፀው ከዚህ በኋላ የሚታዘዘው የማይፈፀም ከሆነ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተወክለው ለመጡት ለአቶ ፀጋአብ ተነግሯቸዋል።
በዚህም መሰረት እጅግ ቢዘገይ እስከ ሚያዚያ 18/2009 ባለው ቀን ውስጥ ከኢብኮ የመጡት ሃላፊ ሃላፊነቱን ወስደው የትርጉም ስራው በፅሁፍ እንዲሰራ እንዲያደርጉ እና በፅሁፍ ለፍ/ቤቱ እንዲያስገቡ ፤ እንዲሁም አቃቤ ህግ እና የተከሳሽ ጠበቆች በተተረጎመው ሰነድ ላይ ያላቸውን አስተያየት ከሚያዚያ 18/2009 በኋላ በቢሮ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቷል። ብይኑን ለመስማት ለግንቦት 7/2009 ቀጠሮ ተይዟል።
2. ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ፍርድ ለመስጠት በሚል ቀጠሮ ተሰጥቶበታል (ሚያዝያ 20/2009 )
የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ማስረጃዎችን ሰምቶ ያጠናቀቀው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በመዝገቡ ላይ የፍርድ ውሳኔ ለማሳለፍ በሚል ብቻ ለ3ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው በዚሁ በሚያዝያ ወር ነው፡፡
ፍ/ቤቱ ብይኑን ላለመስራቱ የሰጠው ምክንያት ‹‹ተከሳሹ የካቲት 30/2009 ዓ.ም በችሎት የሰጠው የተከሳሽነት መከላከያ ቃል ከድምጽ ወደ ጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አልተያያዘልኝም›› የሚል ነበር፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ ፍርድ ለመስጠት በሚል ለ3ኛ ጊዜ ለግንቦት 16/2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡
3. ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ አቅርበዋል
በፌደራል አቃቤ ህግ የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸውን ሚያዝያ 16/2009 ዓ.ም በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ያስገቡት መቃወሚያ 11 ገጾች ያሉት ነው፡፡
በ1ኛ ክስ ጉዳያቸው በሌሉበት ከሚታየው 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሽ ጋር አንቀፅ 238(1) እና (2) ስር በመተላለፍ የተመለከተውን በመተላለፍ የቀረበውን ክስ በተመለከተ፤ ዶ/ር መረራ ከተጠቀሱት ተከሳሾች ጋር ምንም አይነት ድርጅታዊ ቁርኝት ጉዳይ ባለመኖሩ የቀረበባቸው የክስ ጭብጥ ተነጥሎ እንዲታይ በመቃወሚያው ላይ ተጠይቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 01/2009 አንቀፅ 2(1) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ለብቻቸው የቀረበባቸውን 3ኛ ክስ በተመለከተ፤ ዶ/ር መረራ ከየትኛውም የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው እና በሽብርተኝነት ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋርም ምንም ግንኙነት ኖሯቸው እንደማያውቅ ተገልፇል።
የወንጀል አንቀፅ 486(ለ)ን በመተላለፍ ለብቻቸው የቀረበቸውን 4ኛ ክስ በተመለከተ፤ "የሃሰት ወሬን ለማውራት በማሰብ" በሚል የቀረበው ክስ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር የሚያያዝ እንጂ ሃሰተኛ ወሬን መንዛት እንዳልሆነ፤ እንዲሁም በ2006 ተፈፀመ የተባለ ወንጀልን አቃቤ ህግ እድካሁን ድረስ ማስረጃውን ይዞ ማቆየቱ የክሱን እውነትነት እንደሚያጠራጥር በመቃወሚያው ላይ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ በዶ/ር መረራ ላይ የቀረቡት ክሶች በወንጀል ክስ አግባብ መሰረት ተሟልቶ ያልቀረቡ በመሆኑ ሁሉም ክሶች ውድቅ ተደርገው በነፃ እንዲሰናበቱ ተጠይቋል።
የክስ መቃወሚያውን የተቀበለው ችሎት በበኩሉ በቀረበው መቃወሚያ ላይ የአቃቤ ህግን መልስ ለመቀበል ለሚያዚያ 26/2009 ቀጠሮ በመያዝ በዕለቱ መልሱን በጽሁፍ ተቀብሏል፡፡ አቃቤ ህግ በሰጠው መልስም በተከሳሽ በኩል የቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
በተከሳሽ ዶ/ር መረራ ጉዲና የቀረበውን መቃወሚያ እና በአቃቤ ህግ የተሰጠውን አስተያየት መርምሮ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ለግንቦት 25/2009 ቀጠሮ ሰጥቷል።
4. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ ተቃውሞዎችን በተመለከተ የምርመራ ሪፖርት አውጥቷል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2008 እና 2009 ዓ.ም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበው በዚሁ በሚያዝያ ወር ላይ ነበር፡፡ የምርመራ ሪፖርቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ለም/ቤቱ ባቀረበው ሪፖርቱ እንዳመለከተው ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በአጠቃላይ 669 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ለተቃውሞዎቹ በመንስኤነት የተቀመጠው በመንግስት በኩል ያለው የመልካም አስተዳደር እጦት ሲሆን፣ ተቃውሞዎችን በማባባስ ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙ የሳተላይት ሚዲያዎችንና ማህበራዊ ሚዲያን ተጠያቂ አድርጓቸዋል-ኮሚሽኑ በሪፖርቱ፡፡
5. የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፤ በጉብኝታቸው ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸው የነበሩ አካባቢዎችን እንዳይጎበኙ ተከልክለዋል
ከሚያዝያ 24-26 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዘይድ ራዒድ በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽነሩ በሀገሪቱ ሰብዓዊ መብት አጠባበቅና የሚዲያ ነጻነት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የታወቀ ሲሆን፣ በቅርቡ የህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸው የነበሩ አካባቢዎች (ኦሮሚያና አማራ ክልሎችን) ለመጎብኘት ቢፈልጉም በመንግስት እንደተከለከሉ ተገልጹዋል፡፡ ኮሚሽነር ዛይድ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት በራሳቸው ገለልተኛ ማጣራትና ማረጋገጥም ሆነ አባሪ ማስረጃ ማግኘት አለመቻላቸውን አሳውቀዋል፡፡
6. የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ሚያዝያ 25/2009 ዓ.ም ታስቦ ውሏል
በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሰረት በየዓመቱ ሜይ 3 (ሚያዝያ 25) የሚከበረው የዓለም ፕሬስ ነጻነት ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ዕለቱን አስመልክቶ ባሰፈረው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳባቸውን ከመግለጻቸው ጋር በተገናኘ ከአስር በላይ ጋዜጠኞችና ጦማርያን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ጋዜጠኛና ጦማሪ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው፣ ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ፣ ጋዜጠኛ ካሊድ ሞሃመድ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ፣ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ ጦማሪ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ እና የኢንተርኔት አክቲቪስት ዮናታን ተስፋዬ ይገኙበታል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ክስ ተመስርቶባቸው፣ ነገር ግን ከእስር ውጭ ሆነው ክሳቸው በይደር ያለ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፡-የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፍ ብርሃኔ፣ እንዲሁም ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና አምደኛ አምሳሉ ገ/ኪዳን ናቸው፡፡