ሰላማዊ ትግላችን በምርጫ ቦርድ ህገ-ወጥ ውሳኔና በአገዛዙ የኃይል ርምጃ አይቀለበስም! – በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
በዛሬዉ ዕለት ጥር 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ፤ በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ የደረሰዉን ዘግናኝ ድብደባ፣ እስርና እንግልት በጥብቅ እንቃወማለን። የመንግሥት አስተዳደር ወይም ህግ አለ በሚባልበት አገር እጅግ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የደረሰው ድብደባ የተጀመረዉን ሰላማዊ ትግል ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የታለመ ነዉ ብለን አናምናለን። አገዛዙ አንድነት ፓርቲን እንደ ባዕድ ወይም ጠላት በሚመስል መልኩ ታጣቂ ኃይሎችን በብዛት በማሠማራት በሠልፈኞች ላይ ድብደባና እንግልት ፈፅሞባቸዋል።አገዛዙ በተደጋጋሚ በህጋዊ ፓርቲዎች አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ ግድያና ድብደባ አንዲሁም ዘረፋ በማድረግ መንግሥታዊ ዉምብድናዉን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። አንድነት ከአሁን በፊትም ከፍተኛ መሥዋዕትነት እየከፈለ፣ እልህ አስጨራሽ መራር ሰላማዊ ትግሉን እየመራ ይገኛል። ህወሃት መራሹ አምባገነን የዘውግ መንግሥት በፈጠራቸዉ አሥመሣይ ተቋማት በመገልገል በእጅ አዙር በህዝቡና በሰላማዊ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ውምብድና እየፈፀመ ይገኛል። ምርጫ ቦርድ፣ፖሊስና የደህንነት ኃይል፤እንዲሁም አሥተዳደሩ ባጠቃላይ አንድነትንና ሌሎች አጋር ፖርቲዎችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፉት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።
አገዛዙ ከህገ-ወጥ ተግባሩ ታቅቦ መንግሥታዊ ሥነ ምግባር እንዲዝና ሰላማዊ ፖርቲዎችን የማጥፋትና የማሳደዱን ክፉ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነና የሰላማዊ ትግሉ በር ከተዘጋ ህዝቡ አማራጭ መፍትሄ መፈለጉ ስለማይቀር ለሚፈጠረዉ አገራዊ ቀዉስ የስርዐቱ ኀላፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ አንጠራጠርም።
በመጨረሻም የአንድነት አመራሮች የአካሄዱትን ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ አድናቆታችንን እየገለጽን፤ ይህን ዘግናኝ ግፍና በደል ለማስቆም፣ እንዲሁም የአገዛዙን አፈናና ጭቆና ለመቋቋም፣ ብሎም የህዝቡን ልዕልና ለማስከበር ኢትዮጵያዉያን ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅተዉ በመታገል በህዝባዊ ኃይል አገዛዙን ከማስወገድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም። ስለሆነም ትግላችንን በህብረት አጠናክረን ህዝባዊ ትግሉን ለማቀጣጠል ሁላችንም ቆርጠን እንነሳ፦
በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚደረገዉ ድብደባና ግድያ በአስቸኳይ ይቁም!
ህዝባዊ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል!
በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
የሥራ አመራር ቦርድ
No comments:
Post a Comment