Friday, November 27, 2015


በእዉቁ ከያኒ፤ደራሲ እና የኪነ-ጥበብ ሰዉ ደበበ እሽቱ Debebe Eshetu በፀሐይ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት "ኢትዬዽያ .. የባሩድ በርሜል" በሚል አርእስት ወደ አማርኛ የተተረጎመውን "Abyssinia . The Powder Barrel" መጽሐፍ ፊርማ እና ውይይት በአሻራ አርትስ አዘጋጅነት እሁድ ኖቬምበር 29 ቀን 2015 በታላቋ ቶሮንቶ ከተማ ይካሄዳል፡፡ እኛም በስነስርአቱ ላይ ለመካፈል እንዲሁም የናፈቀንን ወዳጃችን ጋሽ ደቤን በአካል ለማግኘት ጉዞ ወደ ቶሮንቶ ጀምረናል፡፡
"ውጥንቅጧ የወጣው የአሁኗ ኢትዬዽያን ሰለመፈጠሯ በ1935 ዓ.ም እንዴት እንደታስበ ለመረዳት ይህንን መጽሐፍ ማንበብ ወሳኝ ነው"
በዝግጅቱ ላይ መገኘት ለምትፈልጉ
Sunday, November 29, 2015 at Hirut Restaurant 2050 Danforth Avenue, starting from 5pm.

Friday, November 6, 2015



‹‹የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የገዢው ፓርቲ አባል ናቸው›› አትሌት ከላሊ ንጉሴ አብርሃ

የረዥም ርቀት እና ማራቶን ሯጭ ሲሆን አሁን የሚገኘው በስደት ቶሮንቶ፣ ካናዳ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሳለፈውን የህይወት ተሞክሮ በማስመልከት ከኢትዮጵ ዛሬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ኢ.ዛ.፡- በቅድሚያ ይህን ቃለመጠይቅ እንድናደርግ ፈቃደኛ በመሆንክ በትዝታ ጋዜጣ ስም እያመሰገንኩ፤ እሰቲ እራስክን በማስተዋወቅ እንጀምር፡፡ የት እንደተወለድክ ፣ ሙያህን እና የአስተዳደር ሁኔታክን ግለፅልኝ
አትሌት ከላሊ፡- ከላይ ንጉሴ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ራያ ከሚባል አካባቢ ሲሆን ትንሽዬ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ እድገቴም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሲሆን እዛው ራያ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርቴንም ቢሆን እስከ ሁለተኛ ደረጃ እዛው ነው የጨረስኩት፤ በሙያ ደግሞ የረዥም ርቀት እና የማራቶን ሯጭ ነኝ፡፡

ኢ.ዛ.፡-ትንሽ ስለ ራያ ህዝብ እና አካባቢው ብትነግረኝ?
አትሌት ከላሊ፡- ራያ የሚገኘው በትግራይ ክልል ሲሆን፤ በህዝብ ቁጥር እንዲሁም በመሬት ይዞታው በክልሉ ደረጃ ሰፊ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የራያ ህዝብ ዋነኛ መተዳደያው በእርሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰፋ ያለ ይዞታ ቢኖረውም ህዝቡ ግን ከፍተኛ የሚባል በደል የደረሰበት ነው፡፡ ራያ በትግራይ ክልል የተካለለ ቢሆንም የተገለለ አካባቢ ይመስላል፡፡ እንደሌሎቹ የትግራይ ግዛቶች የልማት እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም፡፡

ኢ.ዛ.፡- አካባቢው የልማት ተጠቃሚ አይደለም ስትል ምሳሌ ልትጠቅስልኝ ትችላለክ?

አትሌት ከላሊ፡- ለምሳሌ በከተማ እድገት ብንመለከት ማይጨው የራያ ዋና ከተማ ነው፡፡ እንደዋና ከተማነቱ ይኼ ነው የሚባል መሻሻል ወይም እድገት እንዲሁም ለእድገቱ የሚያስፈልጉ ከመንግስት የሚደረጉ አቅርቦቶች የሉም፡፡ ሌሎች በትግራይ ክልል የሚገኙ አካባቢዎችን ብንመለከት ልዩነቱን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያክል አዲግራት ወይም ኡቅሮ የሚባሉ አካባቢዎች በአማካይ አንድ አይነት የህዝብ ቁጥር እና የመሬት ስፋት ይዘው ግን በመሀከላቸው ያለው የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ አንድ መሰረተ ልማት ብናነሳ እንኳን፣ ህክምናን ብንመለከት በራያ አካባቢ ማይጨው የሚባል ቦታ ላይ አንድ መካከለኛ የሚባል ሆስፒታል ነው የሚገኘው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ይኸው አሁን ከ20 አመት በላይ አሳልፏል፤ ራያን በሚያክል አካባቢ አንድ ክሊኒክ ብቻ፣ አስበው ከተለያዩ የራያ ክፍሎች ሰው ታሞ የሚመጣው እዚችው ሀኪም ቤት፣ እዛ ድረስ እስኪደርስ ያለውን እርቀት፣ መንገድ ላይ የሚሞትም አለ፣ እንደዛም ሆኖ ብትደርስ ብዙ ጊዜ ወደሌላ የትግራይ አካባቢዎች ለሚገኝ ሆስፒታል ሪፈር ትደረጋለክ፡፡ የሌሎች አካባቢ እንቅስቃሴዎችን የማየት እድሉን ስላገኘው ከራያ ጋር ሳመዛዝነው ውስጤ ያዝናል፡፡ ይኼም ሳያንስ መንግስት እንዲህ እና እንዲያ እያደረኩ ነው ብሎ በሚዲያ ሲናገር ጉዳዩን ለምናውቀው የሚያሳዝን ነው፡፡

ኢ.ዛ.፡-በቋንቋ ስንመለከት ራያ በሦስት የተከፈለ ነው ብለው የሚናገሩ አሉ ይኸውም የአማርኛ ተናጋሪ፣ የኦሮምኛ እንዲሁም የትግርኛ ተናጋሪ፤ ሦስቱም አንድ ላይ ተጠቃለው ነው ወይስ እንደቋንቋቸው አካባቢያቸውም ይለያያል?

አትሌት ከላሊ፡- ራያን በአጠቃላይ ስንመለከተው በሁለት ልንከፍለው እንችላለን፤ ይኸውም ራያ ቆቦ የሚባለው ወደ አማራ አካባቢ የሚገኘው ሲሆን በአብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪ ያለበት ክፍል ሲሆን፤ እኔ ወደምኖርበት አካባቢ ያለው ደግሞ ራያ አዘቦ የሚባለው አካባቢ ሲሆን ትግርኛ፣ አማርኛ እንዲሁም ኦሮምኛም ተናጋሪዎች ያሉበት ነው፡፡ እንዲህ ቢከፋፈሉም ያው እንደ አንድ ክልል ነው የሚታወቁት፡፡


 ኢ.ዛ.፡-ወደ አትሌቲክሱ ህይወትክ እንመለስ እና እንዴት ወደ ሩጫው ገባህ?

አትሌት ከላሊ፡- ፕሮፌሽናል የአትሌቲክስ ህይወት የጀመርኩት እዛው ራያ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ በጊዜው የከፍተኛ ሁለተኛ ተማሪ ነበርኩኝ ጊዜውም ወደ 1999 ዓ.ም. አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ በጊዜው ከተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ሯጮች በክልሉ በተካሄደው ውድድር ይሳተፉ ነበር፡፡ እኔም የምኖርበትን ወረዳ በመወከል ለመሳተፍ በቃሁ፡፡በጊዜው ጥሩ የሚባል ሰዓት በማስመዝገቤ ከዛን ጊዜ በኋላ በሌሎች ውድድሮችም እንድሳተፍ ተደረኩኝ ማለት ነው፡፡

ኢ.ዛ.፡-እንደሚታወቀው እትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በብዙ የሚቆጠሩ ወጣት አትሌቶችን ታፈራለች፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ችሎታ ኖሯቸው እንኳን እድሉን አግኝተው ወደ ከፍተኛ መድረኮች ወጥቶ ለመወዳደር በራሱ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንባቸው በየጊዘው የሚሰማ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ አንተም ከእነሱ አንዱ እንደመሆንክ እንዴት እድሉን አገኝተክ ልትወጣ ቻልክ?

አትሌት ከላሊ፡- እርግጥ ነው ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፤ የኔም ጉዳይ ቢሆን እድል ተጨምሮበት እንጂ ሚናልባትም እዛው እቀር ነበር፡፡ ወረዳ ላይ ከተሳተፍኩ በኋላ ሌሎች ውድድሮችም ላይ አመርቂ ውጤት በማስመዝገቤ የትግራይ ክልልን ወክዬ እንድሳተፍ ተደረኩኝ፡፡ ከዛም ወደ አዲስ አዲስ አበባ በመምጣት ትግራይን ወክዬ ተወዳድሬያለሁ፡፡ በይበልጥ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2002/2003 ዓ.ም. ጥሩ ፐርፎርማንስ አሳይቼ ነበር በዚህም የተነሳ ማረሚያ ለሚባል የስፖርት ክለብ ውስጥ ለመሮጥ በቃሁ፡፡ እዛ በነበርኩበትም ወቅት በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተሳተፍኩ ሲሆን ይኸውም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በበርካታ መድረኮች ላይ ለመወዳደር ችያለሁ፡፡

ኢ.ዛ.፡-በተለያዩ ሀገራት የመወዳደር እድል እንዳገኘክ ነግረኸኛል፤ እንዴት ነበር በግልክ ነው ወይስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመቻችቶልክ ነው?

አትሌት ከላሊ፡- በእርግጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው በውድድሩ ላይ እንድንሳተፍ የሚያደርገው፡፡ ይሁን እንጂ የምትወዳደርለትን ክለብ ወይም ሀገርህን አልያም ደግሞ በግልቅ መሳተፍ ትችላለክ፡፡ ዋናው ነገር በቅርብ ጊዜያት የምታስመዘግበው ውጤት ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ በረዢም ርቀቶች ላይ ስትሳተፍ ቢያንስ ጥሩ ሰዓት እና ከ1-7 ወይም እስከ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚወጡት ሯጮች ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡ ሀገር እንዲወክሉ ይደረጋል ማለት ነው፡፡

ኢ.ዛ.፡-ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በተያያዘ በርካታ መረጃዎችን እንሰማለን፤ ይኸውም እኩል የሆነ እድል ለሯጮች አይሰጥም፣ በሙስና የተጨማለቀ ነው፣ በብሔር የተከፋፈለ ነው፣ ሯጮች በሀገር ውስጥ እድል ሳይሰጣቸው ለሌላ ሀግር እየሮጡ ውጤት እያመጡ ነው እና የመሳሰሉ ቅሬታዎችን፤ ከዚህ አንፃር አንተስ የታዘብከው ወይም የደረሰብክ ነገር አለ?

አትሌት ከላሊ፡- በቅድሚያ የሰማኸው መረጃ ትክክል መሆኑን እኔው እራሴ ላረጋግጥልክ እወዳለው፡፡ ያው በየጊዜው የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ እንደው በቅርቡ እዛ በነበርኩበት ጊዜ የተከሰተውን አንድ ጉዳይ ብነግርክ፤ የሴቶች የረጅም ሩጫ ተካሂዶ ነበር፡፡ ታዲያ ውጤት ያመጡትን ይመርጣሉ ብለን እየጠበቅን 2ኛ ነው 3ኛ የወጣችውን ጥለው ውድድሩ ላይ አቋርጣ የወጣችውን ተወዳዳሪ መርጠዋል፡፡ እሷም ሄዳ ውጤት አላመጣችም በውድድሩ 24ኛ ነበር የወጣችው፡፡ ይህ እንግዲህ እኔ በቅርቡ የታዘብኩትን ነው የነገርኩህ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፌዴሬሽኑ ምን ያክል በዝምድና፣ በሙስና፣ በብሔር እና በፖለቲካ አቋምህ እንደሚወሰን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አትሌቲክሱ አያድግም፣ ለታዳጊዎች እድል አይሰጡም ከዚህ የተነሳ ይኸው የድሮ ዝናውን እያጣ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ብዙ ችግር አለበት፤ እውነተኛ ነገር እየተሰራ አይደለም፡፡ የመወዳደር አቅም እና ችሎታ እያለክ፣ ውድድር አግኝተክ፣ ኢንቪቴሽን ወረቀት መጥቶልክ እንኳን በውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ብር ጉቦ መስጠት አለብክ፡፡ ይህን ደግሞ ማድረግ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

 ኢ.ዛ.፡-እንደገለፅክልኝ ይህ የሚያሳየው በፌዴሬሽኑ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ችግር እንዳለ ነው፡፡ ታዲያ አትሌቶቹስ ይኼን እያዩ እንደው ዝም ብለው ያልፋሉ፤ ተሰባስበው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለ ከዚህ አንፃር?

አትሌት ከላሊ፡- የአትሌቶች ማህበር የተቋቋመ አለ፡፡ ሁሉንም አትሌቶች ያቀፈ ማለት ነው፡፡ ሰብሳቢዎቹም ትላልቅ የሚባሉ አትሌቶች ናቸው፡፡ በየጊዜው ስብሰባ ይደረጋል፣ ችግሮች ይነሳሉ፣ መፍትሄ ተብሎ ይወራል ነገር ግን እስካሁን ምንም ሊፈጥሩ አልቻሉም፡፡ አሁንም ችግሮቹ እንዳሉ ናቸው፡፡

ኢ.ዛ.፡-ፌዴሬሽኑ ከገዢው ፓርቲ ጋር በተያያዘ ባለው የፖለቲካ ትስስር ሲታማ ይሰማል፡፡ ለምሳሌ የቴክኒካል ዳይሬክተሩ አቶ ዱቤ ጁሎ የኢህአዴግ አባል መሆናቸው በራሱ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንተ ምን አስተያየት አለህ?

አትሌት ከላሊ፡- እውነቱን ለመናገር ዳይሬክተሩ ብቻ ሳይሆኑ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የገዢው ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ ምንመ እንኳን ፌዴሬሽኑ ከፖለቲካ ገለልተኛ አካል በመሆን መስራት ሲገባው አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ ማናቸውንም ጥያቄዎችን ማንሳትም ሆነ ወደ በላይ አካል ማቅረብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ አንደኛ ሁሉም የተሳሰሩ ስለሆኑ ምላሽ አታገኝም፤ ድምፄን አሰማለሁ ያልክም እንደሆነ የፖለቲካ ታፔላ ተለጥፎብክ ሌላ ችግር ይደርስብካል፡፡

ኢ.ዛ.፡-አንተ እንደ አንድ አትሌት ለዚህ መፍትሄው ምንድነው ትላለክ?
አትሌት ከላሊ፡- በርግጥ እኔ ፖለቲካኛ ስላልሆንኩና ብዙ ፖለቲካ ስላማላውቅ እንዲህ ነው ብዬ ስፊ ትንተና ልሰጥህ አልችልም፡፡ ግን እርግጠኛ ሆኜ የምነግርክ መንግስት ከአትሌቲክሱ ውስጥ ጣልቃገብነት ማቆም አለበት፡፡ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ካልመጣ በፌዴሬሽኑ አካባቢ ብቻውን ለውጥ ይመጣል ወይ የሚለው ነግር ለመመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን በአትሌቲክስም ይሁን በሌላው የህይወት መስክ ወጣቱም፤ የሚቀጥለው ትውልድም ይኼን ስርዓት በርትቶ መታገል አለበት ነው የምለው፡፡ ሌላ ምንም አማራጭ የለኝም፡፡

ኢ.ዛ.፡-በመጨረሻ እንደው ሌላ የምትጨምረው ወይም የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ?
አትሌት ከላሊ፡- በይበልጥ ወጣቱ የተወሰደበትን የእኩልነት እና የነፃነት መብቱን፣ ለእውነት እና ለማንነቱ መታገል አለበት፡፡ ሰው በድህነቱ በብሔሩ ወይም በፖለቲካ አስተሳሰቡ ሲጨፈጨፍ ዝም ብሎ መመልከት ሳይሆን አንድ ሆኖ መታገል አለበት፡፡ ሁሉም በሚችለው አቅሙ ማለት ነው፡፡

ኢ.ዛ.፡-ስለሰጠሀን ቃለምልልስ እናመሰግናለን፡፡

አትሌት ከላሊ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Tuesday, October 20, 2015

Eskinder Nega Wins 2015 PEN Canada One Humanity Award

Eskinder Nega wins PEN Canada One Humanity award at 36th International Festival of Authors

http://pencanada.ca/wp-content/uploads/2015/10/Screen-Shot-2015-10-19-at-1.48.31-PM-628x340.pngTORONTO, Oct. 19, 2015 – The Ethiopian journalist Eskinder Nega will receive PEN Canada’s One Humanity Award on the opening night of the 36th International Festival of Authors (IFOA 36). The award, valued at $5,000, is presented at PEN’s annual gala to a writer whose work transcends the boundaries of national divides and inspires connections across cultures.

Mr. Nega, an independent journalist, was arrested in September 2011 under the provisions of Ethiopia’s Anti-Terrorism Proclamation for criticizing the detention of a prominent government critic, and disputing the government’s assertion that detained journalists were terror suspects. At his trial the judge reportedly accused Nega of using “the guise of freedom” to “attempt to incite violence and overthrow the constitutional order” through a popular revolt similar to those of the Arab Spring.
Convicted on June 27, 2012, Nega was sentenced to 18 years in prison. In December 2012 the United Nations Working Group on Arbitrary Detention said the sentence violated free expression and due process rights under international law. The UN group called for his immediate release. On May 2, 2013, the Ethiopian Federal Supreme Court upheld both the conviction and the sentence.
Nega is one of eight journalists and bloggers currently jailed in Ethiopia under the Anti-Terrorism Proclamation, according to PEN International’s case list. Six others were released in July 2015 after being held for periods ranging from 16 months to four years under the same legislation.
Since its 2010 UN Universal Periodic Review (UPR), Ethiopia has repeatedly used its Anti-Terrorism Proclamation to arbitrarily arrest, prosecute, and imprison independent journalists and opposition activists. Ahead of Ethiopia’s 2014 UPR, a shadow report by PEN International and the Committee to Protect Journalists found the Proclamation overbroad and inconsistent with international law. The use of the Anti-Terror Proclamation to stifle the independent media has been condemned both by regional human rights bodies and the UN.
The Ethiopian government has arbitrarily imposed restrictions on the distribution of broadcast and print licenses, the content and editorial position of news outlets, the freedom of movement of journalists, the accreditation of international journalists, and domestic access to international broadcasts and Internet content.
Since 1992, government pressure has forced at least 75 independent publications, overwhelmingly from the Amharic language press, to close. Although a large number of private publications continue to operate, less than a handful of publications cover politics with a critical perspective. A high number of journalists have fled the country as a result of government persecution.
Photo credit: Lennart Kjorling
http://pencanada.ca/news/eskinder-nega-wins-2015-pen-canada-one-humanity-award/

Wednesday, August 19, 2015

Saturday, August 8, 2015

Monday, April 13, 2015

Sunday, January 25, 2015

10298794_640348846050053_3108728034139348229_n

ሰላማዊ ትግላችን በምርጫ ቦርድ ህገ-ወጥ ውሳኔና በአገዛዙ የኃይል ርምጃ አይቀለበስም! – በሰሜን  አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር

በዛሬዉ ዕለት ጥር 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ፤ በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ የደረሰዉን ዘግናኝ ድብደባ፣ እስርና እንግልት በጥብቅ እንቃወማለን። የመንግሥት አስተዳደር ወይም ህግ አለ በሚባልበት አገር እጅግ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የደረሰው ድብደባ የተጀመረዉን ሰላማዊ ትግል ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የታለመ ነዉ ብለን አናምናለን። አገዛዙ አንድነት ፓርቲን እንደ ባዕድ ወይም ጠላት በሚመስል መልኩ ታጣቂ ኃይሎችን በብዛት በማሠማራት በሠልፈኞች ላይ ድብደባና እንግልት ፈፅሞባቸዋል።
አገዛዙ በተደጋጋሚ በህጋዊ ፓርቲዎች አመራር አባላትና ደጋፊዎች ላይ ግድያና ድብደባ አንዲሁም ዘረፋ በማድረግ መንግሥታዊ ዉምብድናዉን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። አንድነት ከአሁን በፊትም ከፍተኛ መሥዋዕትነት እየከፈለ፣ እልህ አስጨራሽ መራር ሰላማዊ ትግሉን እየመራ ይገኛል። ህወሃት መራሹ አምባገነን የዘውግ መንግሥት በፈጠራቸዉ አሥመሣይ ተቋማት በመገልገል በእጅ አዙር በህዝቡና በሰላማዊ የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ውምብድና እየፈፀመ ይገኛል። ምርጫ ቦርድ፣ፖሊስና የደህንነት ኃይል፤እንዲሁም አሥተዳደሩ ባጠቃላይ አንድነትንና ሌሎች አጋር ፖርቲዎችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፉት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።
አገዛዙ ከህገ-ወጥ ተግባሩ ታቅቦ መንግሥታዊ ሥነ ምግባር እንዲዝና ሰላማዊ ፖርቲዎችን የማጥፋትና የማሳደዱን ክፉ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነና የሰላማዊ ትግሉ በር ከተዘጋ ህዝቡ አማራጭ መፍትሄ መፈለጉ ስለማይቀር ለሚፈጠረዉ አገራዊ ቀዉስ የስርዐቱ ኀላፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ አንጠራጠርም።

በመጨረሻም የአንድነት አመራሮች የአካሄዱትን ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ አድናቆታችንን እየገለጽን፤ ይህን ዘግናኝ ግፍና በደል ለማስቆም፣ እንዲሁም የአገዛዙን አፈናና ጭቆና ለመቋቋም፣ ብሎም የህዝቡን ልዕልና ለማስከበር ኢትዮጵያዉያን ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅተዉ በመታገል በህዝባዊ ኃይል አገዛዙን ከማስወገድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም። ስለሆነም ትግላችንን በህብረት አጠናክረን ህዝባዊ ትግሉን ለማቀጣጠል ሁላችንም ቆርጠን እንነሳ፦

በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚደረገዉ ድብደባና ግድያ በአስቸኳይ ይቁም!
ህዝባዊ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል!

በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር
የሥራ አመራር ቦርድ

Saturday, January 17, 2015

ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!!
      

ጉዳዩ፥  በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና በአንድነት ፓርቲ መካከል    የተፈጠረውን ውዝግብ በተመለከተ፡፡

እንደሚታወቀው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ባለፈው ሣምንት ከምርጫ ቦርድ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ በ 4 ቀን ውስጥ እንዲጠራና የፓርቲውን መሪ በድምፅ አሠጣጥ መመሪያው መሠረት እንዲመርጥ ስለተገደደ አንድነት ፓርቲም በሆደ ሰፊነት በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ባያምንበትም ሕግ ለማክበርና የሠላማዊ ትግሉን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ስለሚረዳ በሌለ አቅሙ በ 4 ቀን ውስጥ በአስቸኳይና በታላቁ በገና በዓል ሣምንት የጉባዔ አባላትን ከክ/ሃገር ጭምር ጉባዔ ጠርቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፋ በ 4 ቀን ጉባዔ እንዲጠራ ካዘዘ በኋላ በጉባዔው ተገኝቶ ምርጫውን ታዝቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጋብዞ ሣይገኝ ቀርቷል፡፡ ይህ ዓይነት የምርጫ ቦርድ ሕገ-ወጥነት በጥብቅ ሊወገዝ ይገባል፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ምርጫ ቦርድ አሁንም እጅግ በጣም በሚያሳፍርና ይሉኝታ በሌለው አካሄድ አንድነት ፓርቲንና መኢአድን በድጋሜ ጉባዔ እንዲጠሩ ሕገ-ወጥ ትዐዛዝ ለማስተላለፍ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን ውስጥ ጉዳይ የመፈትፈት፣ ውሣኔ የመቀልበስ፣ እንዲሁም የፓርቲዎችን አመራር የማፅደቅ ወይም ያለማጵደቅ መብት ጨርሶ ሊኖረው አይገባም፡፡ ምከንያቱም እንደዚህ ዓይነት ጣልቃ ገብነት ካለ የፓርቲዎች የበላይ አካል የሚሆነው የአባሎቻቸው ጠቅላላ ጉባዔ ትርጉም አልባ ይሆናልና፡፡
አንድነት ፓርቲ በምጫ ቦርድ በድጋሜ የተላለፈውን ጉባዔ የመጥራት ትዕዛዝ እንደማይቀበለው መግለፁን ስንቀበል፤ እኛም የአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበር ሙሉ በሙሉ እንደምንደግፍ እናረናገግጣለን፡፡ ምርጫ ቦርድ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ ለአገዛዙ ወገናዊነትን ለማረጋገጥ በአስተዳደሩ ኃላፊዎች በመታዘዝ፤ በአንድነት ፓርቲና በሌሎች ተቃዋሚ አጋር ፓርቲዎች
የሚያደርገውን ሕገ-ወጥነት አስተዳደራዊ ክፉ ሥራ አጥብቀን እንቃወማለን! አንቀበለውም:: አገዛዙ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ ከፈለገ ህጋዊ የፓለቲካ ፓርቲዎችን በህገ-ወጥነት ሣይሆን በስርዓት፣ በአግባቡ የጨዋታ ሜዳውን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ የተደጋጋሚ ጉባዔ ጥሩ ትዕዛዝ ህገወጥ ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም፡፡ አገዛዙ እንደዚህ ዓይነት እጅግ የዘቀጠ ፀያፍ ስራ
ውስጥ ተነክሮ ያለው መጪውን ብሔራዊ ምርጫ ያለተቀናቃኝ ብቻዉን ተወዳድሮ ለማሸነፍ ካለው ጭፍን ፍላጐት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም ግን ይህ አካሄዱ ሃገሪቱን ወደ ባሰ ምስቅልቅል ይወስዳታል እንጅ ሌላ ፋይዳ የለውም፡ በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ማለትም መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ መድረክና፣ ሌሎችም ፓርቲዎች ተቀራርበው ትግሉን በጋራ እንዲመሩት ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ፓርቲዎቹ አገዛዙን በመቃወም ለሚያደርጓቸው ማንኛውም የሠላማዊ እንቅስቃሴዎች ከጐናቸዉ እንደምንቆም በዚህ እጋጣሚ ማሣወቅ እንወዳለን፡፡ አንድነት ፓርቲ በሚያደርጋቸው የትብብር ጥሪዎችና የአመራር ስልቶች በተናጠልም ወይም ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር ለሚያደርጋቸው ትግሎች ሙሉ በሙሉ የማቴሪያልና የሞራል ድጋፍ እንደምንሰጥ እናረጋግጣለን፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብም የአገዛዙን ተንኮል በመረዳት ከአንድነትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጐን በመሰለፍ የነፃነት ትግሉ እንዲያፋጥን ጥሪ አናቀርባለን፡፡

Monday, December 15, 2014

                    ተደራጅ 2007 ለለውጥ
 



አንድነት በነገው ዕለት ተደራጅ 2007 ለለውጥ የሚል ዘመቻ በሶሻል ሚዲያና መዋቅሩ በዘረጋባቸው የሀገሪቱ አከባቢዎች ሁሉ ይጀምራል! የዚህ ዘመቻ ዓላማ በቀጣዩ ምርጫ ፓርቲው አሸናፊ ሆኖ አንዲወጣ የሚያደርጉት ህዝባዊ ንቅናቂዎች ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፤ ህዝቡ በምርጫው ሂደት ከመጀመሪየው ጀምሮ ተሳታፊ እንዲሆን በፓርቲው በአባልነትና በደጋፊነት እንዲደራጅና በንቃት እንዲሳተፍ ያደርጋል። ህዝቡ ተደራጅቶ ታህሳ 12 በሚደረገው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ላይ ቤቀበሌው በመገኘት ገለልተኛ ሆኑና በህዝቡ ዘንድ ተአማሚነት ያላቸው የህዝብ ታዘቢዎች የመርጣል፤ በቀጣ ደግሞ የምርጫ ካርድ ሁሉም በነቂስ እንዲወስድ ይደረጋል፤ ከዚያ ድምፁ እንዳየጭበረበር የአንድነት ታዛቢ ሆነው የሚያገለገሉ ያዘጋጃል፤ በአጠቃላይ የምርጫው ሂደት በህዝቡ የነቃ ተሳጠፎ ተጀምሮ እስከመጨረሻ ድረስ የዘልቃል ማለት ነው። ይህ ሁሉ ተደርጎ ኢህአዴግ ተሸንፎ እያለ የህዝቡን ድምፅ ለማጠፍ የሚንቀሳቀስ ከሆነ አሁንም የተደራጀው ህዝብ ህዝባዊ እምቢተኘነት በማካሄድ ድመፁን እንዲያስጠብቅና የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ይገዳል ማለት ነው።
 

አንድነት ይህን ትግል በአግባቡ ለመምራትና ይሄ ዓመት የኢህአዴግ መጨረሻ ለማደረግ ቆረጦ ተነሰተዋል። የህዝቡን ድምፅ በምንም ዓይነት ሁኔታ አሳልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም፤ ህዝቡም ቢሆን ድምፁ እንዳይወሰድበት ካሁኑ ከፓርቲው ጎን በመቆም መደራጀትና በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል።
                                                     ድል የህዝብ ነው!

Thursday, November 20, 2014

የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች!
Millions of voice for prisoners of conscience!

የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት አንዱ አካል የሆነው የህሊና እስረኞችን የሶሻል ሚዲያ ንቅናቄ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ዘመቻ ሲሆን ከሚቀጥለው ከእሁድ ከህዳር 14 እስከ 20/2007 የሚቀጥል ፕሮግራም ነው። በዚህ ዘመቻ ሚሊዮኖች የፖለቲካ ይሳተፋሉ፤ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ በሰላማዊ መንገድ የሚታሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም ድምፃቸውን ያሰማሉ፤
ዘመቻው ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለመንግስት መስሪያቤቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጓች ተቋማት፣ ለተለያዩ ሚዲያዎች፣ በE‐mail በsms፣ በinbox ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የህሊና እስረኞች አያያዝና የእስር ሁኔታ፣ የታሳሪዎች ማንነትና አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ወዘተ በመግለፅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ማድረግ ነው።
በዚህ ዘመቻ የፖለቲካ አመለካከት፣ ቋንቋ ዘርና ሀይማኖት ሳይለየን ሁላችንም መሳተፍና ድምፃችንን ማሰማት ይኖርብናል። ሳምንቱን ሙሉ ሁሉም የህሊና እስረኞች የሚመለከት ቅስቀሳና ዘመቻ ሲኖር በተለየ ሁኔታ ደግሞ በየቀኑ የሚታወሱ የህሊና እስረኞች ይኖራሉ፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።
እሁድ፦ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮነን እና ሌሎች የአንድነት አባላት
ሰኛ፦ እስክንድር ነጋ እና ርዕዮት አለሙ
ማክሰኛ፦ አብርሃ ደስታ የሽዋስ አሰፋ እና ሀብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሽበሺ
ሮብ፦ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳና ሌሎች የኦሮሞ ታሳሪዎች
ሀሙስ፦ ተመስገን ደሳለኝ እና ውብሸት ታዬ
ዓርብ፦ የሞስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ እነአቡበከር
ቅዳሜ፦ ዞን ዘጠኝ
 

የሳምንቱ መሪ መፈክር የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች!
Millions of voice for prisoners of conscience! የሚል ሲሆን በየቀኑ በተለየ ሁኔታ የሚቀነቀኑት መፈክሮች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው
እሁድ ማክሰኞ እና ሮብ የሚኖሩት መሪ መፈክሮች፦
በሽብርተኝነት ሽፋን ሰላማዊ ታጋዮች ማሰር ይቁም
የህሊና እስረኞች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም
የሽብር አዋጁ ይሰረዝ
መንግስታዊ ሽበራ ይቁም
የዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመደራጀት መብት ይከበር
ሰኞ እና ሀሙስ የሚኖሩት መሪ መፈክሮች፦
Because I am Journalist!
ጋዜጠኞች ማሰርና ማሳድድ ይቁም
ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት ይከበር
ዓርብ ዕለት የሚኖሩ መሪ መፈክሮች፦
የኃይማኖት ነፃነት ይከበር
የሞስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ይፈቱ
መንግስት በማህብረ ቁዱሳን ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ያቁም
መንግስት በኃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ አይገባም የሚለው የህገ መንግስቱ ድንጋጌ ይከበር
ቅዳሜ ዕለት የሚኖሩ መሪ መፈክሮች፦
ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ ይከበር
Blogging Is Not A Crime
ሀሳበን የመግለፅ መብት ይከበር
እንደአስፈላጊነቱ ሌሎችም መፈክሮች ይኖራሉ።

Friday, July 11, 2014




                                                                                                                                                    
                                                
                             ትግሉ የጥቂቶች ሳይሆን የሚሊዮኖች ሆኗል።
                     የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር

በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉጉትና ምኞት ፣ ልጆችዋ ከርሷ የሚሰደዱባት ሳይሆን የተሰደዱት ተመልሰው ለሌሎች መጠጊያ የምትሆን፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ጾታና መደብ ሳይባል ለሁሉም እኩል የሆነች፣ አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ነገር ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገዛዙ እያየን ያለነው፣ ልብን የሚያደማና የሚያቆስል ነው። በስድሳዎቹ ከነበረው የደርግ ስርዓት በባሰ፣ አገዛዙ ሕዝባችን ላይ የግፍ ቀንበር ጭኖ ፣ የጸረ-ሽብርተኝነት ሕግ በሚል ሰበብ ሰላማዊ ዜጎችን እያሸበረ ነው።

የአንድነት ፓርቲ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ በሚል መርህ፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፣ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲቆም በመቀስቀስ፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ድርጅታዊ ሥራ በመስራት፣ በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረገ እንዳለ ይታወቃል። በቅርቡም ከመኢአድ ጋር የቅድመ ዉህደት ስምምነትን በመፈረም የዴሞክራቲክ ካምፑን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ ይቻል ዘንድ፣ ትልቅ ሥራ ተሰርቷል። እነዚህ አገረ ሰፊ እንቅስቃሴዎች፣ አገዛዙን አስደግጠውታል ፣ አሸብረውታልም። ሥር እየሰደደ በመጣዉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድምጹን እያሰማ የመጣዉን የሕዝብ ጥያቄ፣ በአክብሮት ከመመለስ ይልቅ፣ አገዛዙ ከሕዝብ ጋር መላተምን መርጧል። በሕዝብ ዘንድ ከበሬታና ተወዳጅኘት ያላቸውን፣ በሰላማዊነታቸውና በአገር ወዳድነታቸው የሚታወቁትን ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ ወጣት ጋዜጠኞችን እና ብሎገሮች፣ የዲሞክራሲ አክቲቪስቶችን በማሰርና በማስፈራራት ፣ ለነጻነት የሚደረገዉን እንቅስቅሴ ለመግታት ብሎም የሕዝቡን ድምጽ ለማፈን ደፋ ቀና እያለ ነው።
በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ግብረ ኃይል፣ የመኢአድና አንድነት የውህደት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ም/ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አባልና ታዋቂ ብሎገር አቶ አብርሃ ደስታ እና ወገኖችን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ እስርቤት ጥሎ ማሰቃየቱን አገዛዙ በሰፊው መያያዙ በጣም አሳዝኖናል። አስቆጥቶናልም።

የተቀናጀ ህገወጥ ድርጊቶችን የምንኮንነዉና የምናወግዘው ሲሆን፣ አገዛዙም በሕዝቡ ላይ ጦርነት ማወጁን በገሃድ የሚያመላክት እንደሆነ ለማየት ችለናል።በአሁኑ ጊዜ የሕዝቡ ስነልቦና ተቀይሯል። ኢትዮጵያዉያን ግፍን ለመሸከም የሚችሉበት ትከሻ የላቸውም። ጥቂት ወጣት የሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን በማሰር፣ ሕዝቡን አስፈራርቶና መብቱን ረግጦ የመግዛት ዘመን አልፏል። ትግሉ የጥቂቶች ሳይሆን የሚሊዮኖች ሆኗል። በአገር ውስጥና ከአገር ዉጭ ሕዝባዊና ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻው ይጧጧፋል። አገዛዙ በያዘው ብረትና በፈረንጆች ድጋፍ ይመካሉ። እኛ ግን በዉስጣችን ባለው ኢትዮጵያዊ ወኔ፣ በገዛ ክንዳችን እና በፈጣሪ ረድኤት እንመካለን። አገዛዙ ጥላቻን እና ጭካኔን፣ ዘረኝነትን እና መከፋፈልን ይሰብካል። እኛ ግን ፍቅርን እና መቻቻልን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን እንሰብካለን።
በርግጥ የታሰሩ ወጣት የፖለቲካ መሪዎች ወደ ወህኒ መዉረድ ሁላችንንም ያሳዘነና ያስቆጣ ቢሆንም ታሳሪዎቹ ግን ፣ እንደ ክብር ነው የሚያዩት። የነርሱን መፈታት እና ለነርሱም አጋርነታችንን ማሳየት ከፈለግን፣ ማድረግ የሚኖርብን ፣ ከዝምታ ወጥተን፣ የፍርሃትን ካባ አዉልቀን፣ ከሚሊዮኖች አንዱ መሆን ነው። ቆመን፣ ተዋርደን፣ ፈርተን እና ተሸማቀን ከመኖር፣ የሕሊና ነጻነት አግኝተን በአካል መታሰር ይሻለናልና።

በአገር ቤት ያሉ የፖለቲካ መሪዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት በዚህ አጋጣሚ እያደነቅን፣ ከነርሱ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ከመቼዉም ጊዜ በላይ የሰላም ትግሉን እንደምንደግፍ ለማረጋገጥ እንወዳለን። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከሽብር ድርጊቶቹ በአስቸኳይ ተቆጥቦ፣ አራቱ ወጣቶችን ጨምሮ የታሰሩ የሕሊና እስረኞችን በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታ፣ የሕዝብን ጥያቄ ለራሱ ሲል እንዲያከብር እናስገነዝባለን። አገር በዱላና በጡንቻ አትገነባም። አገር የምትገነባው በፍቅር፣በመቻቻልና በመግባባት ነው። የአገዛዙ መሪዎች ልቦናቸውን ለፍቅር ያስገዙ እንላለን። እምቢ ካሉ፣ ካከረሩ ግን ታሪክ እንደሚያስተምረው አወዳደቃቸው እጅግ ታላቅ እና አስከፊ እንደሚሆን ልናስጠነቅቃቸው እንወዳለን።

ኢትዮጵያዉያን ከተባበርን፣ ሁላችንም የድርሻችንን ለማበርከት ከተነሳን፣ ከሚሊዮኖች አንዱ ከሆንን፣ አገዛዙ ፈለገም አልፈለገም የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈታሉ። የተሰደዱ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። የአገራችንን ትንሳኤ እናውጃለን።
የሰላም ትግሉ ተቀናጅቶና ተጠናክሮ ይቀጥላል!!!
July 11, 2014

Monday, June 9, 2014







በአንድነት እና በመኢአድ መካከል የተደረገው ውህደት በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ – የሰሜን አሜሪካ የአንድነት የድጋፍ ማህበራት

 ሰኔ ፪ 2006
ተሰናክለን ነበር፤ አሁን ግን ጸንተናል!

«ዉጊያዉን ተሸነፍን እንጂ ጦርነቱን አልተሸነፍንም» ነበር ያሉት የፈረንሳዩ የ2ኛው ዓለም ጦርነት መሪ፤ ጀነራል ቻርለስ ደጎል፣ አገራቸው በናዚዎች ሥር በወደቀች ጊዜ። ልክ እንደ ዉትድርናዉም፣ በሰላማዊ ትግል ዉስጥ መሸነፍ፣ መዉደቅ፣ መሳሳት አለ። መነሳትም እንዲሁ፡፡ ታላቁ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እንዳሉትም፤ «በሕይወት ውስጥ ትልቁ ነገር ፈጽሞ አለመውደቅ ሳይሆን፤ በወደቁ ቁጥር መነሳት ነው»
በአገራችን የሰፈነዉን አምባገነንነት በመቃወምና በአገራችን ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ላለፉት አያሌ አመታት ትእግስት አስጨራሽ ትግል ቢደረግም፤ የተደረጉ ጥረቶች የተፈለገውን ዉጤት ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡
በተለይ በምርጫ ዘጣና ሰባት ወቅት፣ በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚያነቋንቅ ትልቅ ሥራ ተሰርቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቅንጅትን በመሰረቱ ድርጅቶች መካከል ልዩነቶች ስለተፈጠሩ፣ የቅንጅት አመራር አባላትም በተለያዩ ምክንያቶች ስለተከፋፈሉ፣ የአገዛዙ አፈናና የረቀቀ ከፋፋይ ሴራ ተጨምሮበት፣ ያኔ የነበረዉ የቅንጅት አብዮት እንዲቀዘቅዝ ሆኗል፡፡። ይህም የአምባገነኖች ደስታ ሆኖ ቆይቷል።
ነገር ግን ደጎል እንዳሉት፤ ለግዜው ተሰናክለን ወደቅን እንጂ ተስፋ አልቆረጥንም። ተነሳን እንጂ፤ ወድቀን አልቀረንም፡፡ ላለፉት ሶስት አራት አመታት የመቀራረብና አብሮ የመስራት መንፈስ በተቃዋሚዎች መካከል ሥር እየሰደደ ሲመጣ ታዝበናል። አገር ቤት አሉ ከሚባሉ ጠንካራ ደርጅት መካከል፣ የአንድነት ፓርቲ፣ ከብርሃን ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጋር ከሶስት አመታት በፊት ውህደት የፈጠረ ሲሆን፣ አንድነት ከሌላው አንጋፋ ድርጅት መኢአድ ጋር ለመዋሃድ ንግግሮችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ሲደረጉ የነበሩ አድካሚ ንግግሮች ፍሬ አፍርተዉ፣ በመኢአድና በአንድነት መካከል የቅድመ ዉህደት ስምምነት ሰኔ አንድ 2006 ዓ.ም ተፈርሟል። ይህ ታሪካዊ ክስተት ለድርጅታችንም ሆነ ለመላዉ ነጻነት ናፋቂ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ደስታና ተስፋ ፈንጣቂ ነው ብለን እናምናለን። የመኢአድና የአንድነት አመራር አባላትን ድርድራቸው ለዚህ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፤ ይህን አይነት መልካም ዜና ስላሰሙንም ልናመሰግናቸው እንወዳለን። ውህደቱም ሙሉ ለሙሉ እንደሚሳካ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ማህበራችን በምኞትና በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር፣ የዚህ ታሪካዊ፣ ወሳኝ ትግል አጋር በመሆን የድርሻዉን እንደሚወጣ በዚህ አጋጧሚ ቃል እንገባለን።
ሌሎችም በሰላማዊ ትግል አገር ቤት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ፣ መኢአድ እና አንድነትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ እያቀረብን፣ በዉጭ ያሉ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ደርጅቶችም ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲሉ ይህን ውህደት እዲደግፉና እንዲሰባሰቡ ጥሪ እናቀርባለን።
አንድነትና/መኢአድ ትግሉን በስሜት ሳይሆን በማስተዋል፣ በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፥ በማራቅ ሳይሆን በማቅረብ እንዲመሩት እንመክራለን። ስህተቶች ይሰራሉ፤ ነገር ግን በስህተቶች የመደናገጥና በቀላሉ ተስፋ የመቆረጥ ዝንባሌያችን አስተካክለን፣ ለፈታኝ እና ወሳኝ ትግል ሁላችንም እንዘጋጅ። ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት እንነሳ።
በአጭር ግዜ የድርጅቱ ሙሉ ውህደት ተጠናቆ፤ ውህድ ድርጅቱ ለመጪው ምርጫም ይሁን ቀጣይ ትግል የሚያዘጋጁ የፖሊሲ ውይቶችን እንደሚጀምር፤ የበሰለ አመራር በመስጠት እንደ 1997ቱ ሁሉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚወጣ እንጠብቃለን፡፡
በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የድጋፍ ማህበራት፤ በሁለቱ ድርጅቶች ደጋፊዎች መካከል ውህደት እንዲኖር እንደምንተጋ፤ እንዲሁም ውህድ ድርጅቱን በገንዘብ፤ በቁሳቁስ፤ በሞራልና በዲፕሎማሲ እንደምንረዳ ቃል እንገባለን፡፡
ነጻነት የትግል ውጤት ነው!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!udJAEUP

Tuesday, April 8, 2014



ቶሮንቶ፤ ከአንድነትና ከነቀምት ከተማ ጎን ይቆማል !!
የአንድነት ቶሮንቶ የድጋፍ ሰጪ ማህበር መግለጫ
ሚያዚያ፤ 2014፤ ቶሮንቶ፤ ኦንቴርዮ

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፤ (ከዚህ በኋላ "አንድነት")፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ፤ ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አዲስ አበባ የሚያበቃ፤ በ17 ከተሞች የሚደረግ፤ የኑሮ ውድነትን፤ የመሬት ባለቤትንትን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈናን፤ የሚመለከቱ የተቃውሞ ሰልፎችን አሰናድቷል፡፡
የመጀመሪው ሰልፍ፤ እሁድ መጋቢት 28 ቀን በአዲስ አበባ እንዲደረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት በፈጠረው ስንኩል ምክንያት ሰልፉ ተጨናግፏል፡፡ በተመሳሳይ ቀን የተጠራው የደሴ ሰልፍ ግን፤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
የአዲስ አበባው ተለዋጭ ሰልፍ፤ ለእሁድ፤ ሚያዚያ 5 ቀን የተቀጠረ ሲሆን፤ ሰልፉ የተሳካ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 
አንድነት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ የሚደርጋቸውን ሰልፎች በገንዘብ ለመርዳት፤ በሲያትል፤ አትላንታ፤ ላስ ቬጋስና ሌሎች ከተሞችም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቃል ገብተዋል፡፡ ቅዳሜ፤ እንደፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ማርች 29 ቀን የተሰበሰበው የቶሮንቶ አንድነት ድጋፍ ሰጪ ማህበርም፤ የነቀምትን ከተማ ሰለፍ ለመርዳት መወሰኑን ሲያስታውቅ በታላቅ ኩራት ነው፡፡     
አንድነት ቶሮንቶ፤ ለነቀምቱ ሰልፍ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ቅዳሜ ኤፕሪል 26 ቀን፤ 2014 ዓ.ም.፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከ3pm ሰኣት ጀምሮ፤ 2050 ዳንፎርዝ ጎዳና ላይ በሚገኘው ሂሩት ካፌ፤ አጋርነት ለነቀምት የተሰኘ፤ መደበኛ ያልሆነ የአንድነት መርሀግብር አዘጋጅቷል፡፡ በቶሮንቶና አካባቢው የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዝግጅቱ ላይ እንድትገኙና የበኩላችሁን የገንዘብ አስተዋጽኦ እንድታደርጉ አንድነት ቶሮንቶ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አንድነት ቶሮንቶ፤ አገር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የተለያዩ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎችን አልፈው የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሰልፋቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት መሰናከል የለበትም የሚል እምነት አለው፡፡ ስለዚህም፤ በዚህ መደበኛ ባልሆነ፤ የአብረን እንዋል ዝግጅት ላይ በመገኘት፤ የበኩልዎን የገንዘብ ልገሳ እንዲያደርጉ ጥሪ እያደረገ፤ በእለቱ በአካል መገኘት ካልቻሉም የገንዘብ ልገሳዎን በሌላ ሰው መላክ እንደሚችሉ፤ እንዲሁም ችሮታዎን በአንድነት የባንክ ሂሳብ Unity for Human Rights and Democracy: TD Trust; የባንክ ሂሳብ ቁጥር፡ 12682 0041 0883 5209213 ማስገባት እንደሚችሉ ይጠቁማል

በዚህ አጋጣሚም፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት (UDHR) ወይም 

በተለምዶ ዩዲጄ ቶሮንቶን እንዲተዋወቁና፤ በአንድነት አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ 

የሚከተለውን ማስታወሻ እናክላለን፡፡

አንድነት ቶሮንቶ ማነው፤ ዋና ዓላማው፤
አንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት (Unity for Democracy and Human Rights) ፤ በኦንቴሪዮ ግዛት የተመዘገበ በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ላይ የሚሰራ፤ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም፤ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግና፤ ኢትዮጵያዊያ ካናዳዊያን በካናዳ ውስጥ የተሳካ ህይወትና ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማበረታታትና መድረክ መፍጠር ነው፡፡

እንድነት ቶሮንቶ እስካሁን የሰራቸው ስራዎች፤

አንድነት ከተመሰረተ ጀምሮ፤ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊን፤ የድጋፍና የምክር አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ካናዳዊያን፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተቃውሞ ሰልፎች፤ በገንዘብ ድጋፍና በዲፕሎማሲ እንዲሳተፉ መድረኮችን ፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ መሪዎች በቶሮንቶና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ከካናዳ ባለስልጣናት ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተነሰራፋውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለካናዳ መንግስት አጋልጧል፡፡ የካናዳ መጤዎችና ስደተኞች ጉዳዮች ባለስልጣን (Immigration and Refugee Board of Canada)፤ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች፤ የጽሁፍ ማብራሪያዎችንና አስተያየቶችን ሰጥቷል፡፡ ለብዙ ስደተኞች የሕይወት ስልጠናዎችንና የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ መድረኮችን ፈጥሯል፡፡ በተለይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸው፤ የካናዳን ጥበቃ እንዲያገኙና ተረጋግተው እንዲኖሩ፤ ባደረገውና በሚያደርገው በገንዘብ የማይተመን ድጋፍ ይኮራል፡፡  

አንድነት ቶሮንቶ አሁን የሚሰጣቸው አገልግሎቶች፡

ያለፉትን አመታት ስራ የገመገመው የአንድነት ቶሮንቶ ስራአስፈጻሚ አካል፤ ድርጅቱ ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ቀዝቀዝ ብሎ እንደነበር አምኖ፤ በቀጣዮቹ ወራት ከላይ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች አስፍቶና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት፤ የሚከተሉትን አገልግሎቶች ለማግኘት ወይም ለመስጠት የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን፤ አንድነትን እንዲያገኙ ወይም እንዲጎበኙ ይበረታታሉ፡፡
ለስደተኞችና አዲስ መጥ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላላ የምክር አገልግሎት መስጠት፤ የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ፤ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን (volunteering) መስራት ለሚፈልጉ ሰዎች መድረኮችን ማመቻቸት፤ የትምህርት ነክ መረጃዎችንና መንገዶችን መጠቆም፤ የካናዳን እወቁ ምክርና የሕይወት ልምድ ልውውጦችን ማዘጋጀት፤ ስደተኞችን መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር ማስተዋወቅ፤ የስራ ጥቆማዎችን መስጠትና ሌሎች መሰል ተግባራትን ማከናወን ናቸው፡፡
ወደካናዳ የመጣ፤ ወይም መምጣት የሚያስብ፤ ዘመድ ወይም ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ካለዎት ከላይ ከተዘረዘሩት፤ ከስራ፤ ከትምህርት እድል፤ ከስደተኝነት ጋር በተያያዘ ጠቅላላ የምክር አገልግሎቶችን የሚፈልጉ ከሆነ፤ አንድነትን ይጎብኙ፡፡ ለተጨማሪ ዝርዝር አገልግሎቶችና መረጃዎች ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ፤ እሁድ ከሰዓት በኋላ በአካል በጽህፈት ቤታችን በመገኘት፤ ወይም ከታች በተጠቀሱት የመገናኛ መንገዶች እንዲያገኙን እናስታውቃለን፡፡

አንድነትን ቶሮንቶን ለማግኘት፤

ኢሜል፤ unityforhumanrights@gmail.com 
በፌስቡክ፤             https://www.facebook.com/unityandnet.andnet
ትዊተር፤   @AndinetToronto                                                 
ስልክ፤     416 422 2962/416 985 6599            
ድረገጽ፤    http://andnettoronto.blogspot.ca/        
የጽህፈት ቤት አድራሻ፡ B2- 2017 Danforth Avenue, Toronto, ዳንፎርዝ ላይ፤ ከዉድባይን ባቡር ጣቢያ በስተምስራቅ 50 ሜትር ራቅ ብሎ፤  ከዘመን እንጀራ መደብር በተቃራኒ፤ ከትብብር መረዳጃ እድር አጠገብ፡፡   
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት፤ የህዝብ ግንኙነት ክፍል፤ ሚያዚያ፤ 2006/2014